+251 114 70 45 33 ዘወትር ከሰኞ - አርብ: 2:30 - 11:30
ለበለጠ መረጃ           

አመሰራረት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በ1879 ዓ.ም የተቆረቆረች ሲሆን 136 ዓመት ዕድሜዋ ላይ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የአስተዳደር ዘይቤዎችንና ስርዓቶችን ስታስተናግድ የቆየች ሲሆን በነዋሪዎቿ የነቃ ተሳትፎ ለከተማዋ እድገትና ለሀገር ግንባታ የበኩሏን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ ያበረከተችና አሁንም በማበርከት ላይ የምትገኝ ናት፡፡

በግንቦት 1997 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ያሸነፈው በወቅቱ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ተብሎ ይጠራ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲ ከተማዋን የማስተዳደር ኃላፊነቱን ለመረከብ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ከሚያዝያ 1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ከተማዋ በጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ስትመራ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም የተሟላ የፖለቲካ ስልጣን ባልነበረበት በያኔው የባለአደራ አስተዳደር ቆይታ በከተማው ተፈጥሮ የነበረውን የአስተዳደር ክፍተት በማጥበብ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እንዲቀጥል ጊዜያዊ ባለአደራ የማይናቅ ሚና ቢጫወትም ቀደም ብለው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመተግበራቸውና የኑሮ ውድነቱም የከተማችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማወክ የህብረተሰቡን ችግር ይበልጥ ማባባሱ የማይዘነጋ እንደነበር መረጃዎች በግልጽ ያሳዩናል፡፡

በሚያዝያ 2000 ዓ.ም በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫም በወቅቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ የህዝቡን ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት በማሸነፉ ከተማዋን የማስተዳደሩን ስልጣን ሊረከብ ችሏል፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ህገ መንግሥት አንቀጽ 49፣ በአዋጅ ቁጥር 361/1995 ተሻሽሎ በወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም ትክክለኛውን የምክር ቤት ቅርፅ የያዘ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተመሰረተ፡፡

ምክር ቤቱ እንደ ህዝብ እንደራሴነት ራሱን ችሎ ሲቋቋም የመጀመሪያው ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማለትም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ከተማ አቀፍ ህጐችን በማውጣት ለከተማዋ ነዋሪ ተደራሽ ከማድረግ ጐን ለጐን በከተማው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ከተቋቋሙበት ዓላማና ተልዕኮ አንፃር ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል እየተከታተለ ድጋፎችንም ሲሰጥ የቆየና አሁንም የዘወትር ተግባሩን ያለመታተር በማከናወን ላይ የሚገኝ የህዝብ ምክር ቤት ነው ፡፡

....

በኢ.ፌዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 50 ቁጥር 2 መሠረት የፌዴራሉና የክልል መንግስታት ስልጣን ህግ አውጪ (Legislative Body )፣ ህግ አስፈፃሚ (Executive Body) እና ህግ ተርጓሚ (የዳኝነት) (Judiciary) አካላት በሚል የተከፋፈለ ሲሆን በዚህ መሠረትም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማዋ ትልቁ ስልጣንና ህግ አውጪ አካል ሆኖ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በመጀመሪያው ምርጫ ዘመኑ 138 የምክር ቤት አባላት በማካተት የተቋቋመ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 111 አባላት ወንዶች፣ 27 አባላት ደግሞ ሴቶች ነበሩ፡፡ የምክር ቤት አባላት ልየታን በተመለከተ ከ10ሩም ክፍለ ከተማ የተወከሉ ሲሆን እንደየክፍለ ከተማው የቆዳ ስፋትና ህዝብ ብዛት ከ11-14 ተወካዮቻቸውን እየመረጡ የሚልኩበት አግባብ ተፈጥሯል፡፡

የከተማችን የመንግስታዊ ስልጣን አደረጃጀት ባለሶስት እርከን የስልጣን ክፍፍል ስርዓት (Three tier system) የሚከተል በመሆኑ ከከተማ በተጨማሪ የክፍለ ከተማና የወረዳ ምክር ቤቶችም ተቋቁመው በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን በአግባቡ ሲወጡ የነበሩ መሆናቸውን እየጠቀስን ሁሉም በየደረጃው ለመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተግባራት የጐላ ተሳትፎና አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

....

የምክር ቤቱን 1ኛ ምርጫ ዘመን መጠናቀቅ ተከትሎም በ2005 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ በድጋሚ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ በዚህም በምክር ቤቱ የነበሩ 138 መቀመጫ ወንበሮች ያሸነፈው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የነበረ ሲሆን ምክር ቤቱ 40 በመቶ የከተማዋን ምሁር፣ 40 በመቶ የከተማዋን ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እና 20 በመቶ ደግሞ የከተማዋን ነዋሪ ህዝብ እንዲወክል ተደርጐ የተዋቀረ ነው፡፡ ይህም የከተማ ምክር ቤቱ ተጠሪነቱ ለመረጠው የከተማዋ ነዋሪ ህዝብና ለፌዴራል መንግስት ነው፡፡ የህፃናትን ድምፅ ሊያሰሙ የሚችሉ ህፃናትን ለመፍጠር እንዲቻል ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች እንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች በተውጣጡ 200 ህፃናት በተካሄደ ጉባኤ በታህሳስ ወር 2002 ዓ.ም የህፃናት ሞዴል ፓርላማም ተመስርቷል፡፡

...

የ6ኛው ሀገራዊና 3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት በግንቦት 2012 ዓ.ም መካሄድ ቢኖርበትም በመላው ዓለምና በሀገራችን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምክንያት የፌዴሬሽን ምክርቤት በሰጠው የህገ-መንግስት ትርጉም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን የተራዘመ ሲሆን ወረርሽኙን የመቋቋም አቅም በመፈጠሩ ከአንድ ዓመት በኋላ በሰኔ 2013 ዓ.ም ምርጫው እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ ሦስተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት በአዲስ ምዕራፍ በ6ኛው ሀገራዊና በከተማችን የ3ኛው ዙር የምርጫ ዘመን ተመራጭ የም/ቤት አባላት በልምድ፣ በሙያ ስብጥር፣ በትምህርት ደረጃ፣ በብዛህነት ተዋፅኦ፣ በመልካም ፈቃድና ቁርጠኝነት ከም/ቤት የሚጠበቀውን ውጤት ለማረጋገጥ ከፍ ባለ ዝግጅትና ስነ ልቦና ስራውን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ. የጀመረ ሲሆን ለውጡን ማሻገር የሚችል አደረጃጀትና አሰራር ተፈጥሮ በምርጫ ዘመቻ ወቅትና በኋላም በገዥው ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎች ላይ ተመስርቶ ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የም/ቤት መዋቅርና አደረጃጀት በመፍጠር አሰራሮችንና የሰው ኃይል ብቃቱን ለውጡ ከሚፈልገው ተቋማዊ ሪፎርም አኳያ ከፍ ባለ ንቅናቄና ሞራል በርካታ ዝግጅቶች አድርጓል፡፡

...

የተከበሩ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ያሉ የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት በተመለከተ ምክር ቤቱ በመጀመሪያው ምርጫ ዘመኑ የነበረውን የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 2 (ተ) መሠረት ሰባት ቋሚ ኮሚቴዎች በማቋቋም የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ ሥራዎችን ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የም/ቤቱን አሠራር ለመወሰን ባወጣው ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 3/2001 አንቀፅ 11 እና ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት በአምስት ቋሚ ኮሚቴዎችን ማለትም፡- 1. ማዘጋጃቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 2. አቅም ግንባታ ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 3. ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 4. መንግሥት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 5. ህግና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አደራጅቶ አስፈፃሚውን አካል በየዘርፉ በመለየት ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየም በየስራ ዘመኑ የተከናወኑት ተግባራትና የተያዙ የመዛግብት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ አግባብ ሲጓዝ ከቆየ በኋላ በሂደት እያስመዘገባቸው ከሚመጣ ለውጦችና የአሠራር ማሻሻያዎች አንጻር በ2ኛው ምርጫ ዘመኑ በ2007 ዓ.ም የሥራ ዘመን ምክር ቤቱ በ2001 ላይ ባወጣው ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 3/2001 መሠረት ከ5 ወደ 6 የቋሚ ኮሚቴዎችን ቁጥር ከፍ በማድረግ፡-

  • የመንግስት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የከተማ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና
  • የማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎችን በማደራጀት እና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት
የተለመዱ ተግባሮቹን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በሂደት የከተማዋ የመልካም አስተዳደር የልማት ተጠቃሚነት ፍላጐት እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፤ የምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካሉን በአግባቡ የመከታተል፣የመቆጣጠርና የመደገፍ አቅሙም ፍላጐቱም ከፍተኛ በመሆኑ ከታህሳስ 2011 ዓ.ም ወዲህ በማሻሻያ ደንቡ መሠረት ባካሄደው ጥናትና የሌሎች ክልሎች ም/ቤት አመራር ልምድ ልውውጥ ቅመራ በማድረግ የተሻለ አሠራርና ለውጥ ማምጣት በሚያስችል መልኩ የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ከ6 ወደ 7 ከፍ በማድረግ፡-
  • የመንግስት ወጪ በጀት አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጉዳዮች
  • የሰላም፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
  • የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና
  • የመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
አደራጅቶ ምክር ቤቱ የተለመደ አሠራሩን በተቀናጀና በተቀላጠፈ መልኩ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማው ህግ አውጪ ተቋም ነው!

በሚያዝያ 2000 ዓ.ም በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫም በወቅቱ ገዢ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ የህዝቡን ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት በማሸነፉ ከተማዋን የማስተዳደሩን ስልጣን ሊረከብ ችሏል፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ህገ መንግሥት አንቀጽ 49፣ በአዋጅ ቁጥር 361/1995 ተሻሽሎ በወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም ትክክለኛውን የምክር ቤት ቅርፅ የያዘ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተመሰረተ፡፡

ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በስራ ላይ ለማዋል የከተማው ምክር ቤት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አዋጅ የማውጣት ስልጣን አለው፡-

  • የከተማውን አስፈጻሚ አካላት ለማቋቋም፣
  • የከተማውን አስተዳደር በጀት ለማጽደቅ፣
  • የከተማውን መሪ ፕላን ለማውጣት፣
  • በዚህ ቻርተር በተደነገገው መሰረት የከተማውን የዳኝነት አካላት ለማቋቋምና እንደየአግባቡ ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን፣
  • በዚህ ቻርተር መሰረት በከተማው አስተዳደር ስልጣን ስር በሚወድቁ የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ግብር እና ቀረጥ ለመጣል፣የአገልግሎት ክፍያ ለመወሰንና ፣እና
  • በከተማው አስተዳደር የወጡ ነባር ሕጎችን ለመተካት፡፡ የከተማው ምክር ቤት የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፤

ራዕይ

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት በ2022 ዓ.ም ተደራሽነት ያለው ህግ በማውጣትና በማስተግበር ተምሳሌት ከሆኑ አስር የዓለም የከተማ ም/ቤቶች አንዱ መሆን፡፡

ተልዕኮ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያረጋግጡ ከተማ አቀፍ ሕጐችን ህዝቡን አሳትፎ ማውጣት፣ አስፈፃሚ አካላትን በመከታተልና በመቆጣጠር የምክር ቤቱን እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎች በማሳወቅ የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ፡፡

ዕሴቶች

  • የህግ የበላይነትን እናረጋግጣለን፡፡
  • ኪራይ ሰብሳቢነትን እንታገላለን፡፡
  • ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት እናገለግላለን፡፡
  • ለሕዝብ ተጠቃሚነት ተግተን እንሠራለን፡፡
  • በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ መብቶች እንዲረጋገጡ በትጋት እንሰራለን፡፡
  • በምክር ቤቱ የመቻቻል ባህልን እናዳብራለን፡፡
  • የሕዝቡን ውክልና እናረጋግጣለን፣
  • በእምነትና በእውቀት እንሠራለን፣