የተከበሩ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ሐጀዙሊ

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ

የተወደዳችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፤ ስለአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት ከምስረታ ጀምሮ ባጠቃላይ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ስለተሰጠው ስልጣንና ተግባር፣ እንዲሁም ስለተልዕኮው ለእናንተ ለነዋሪዎች በአጭሩ መረጃ ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡
እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት በተሸሻለው የከተማ አስተዳደሩ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 መሰረት ግንቦት 12/2000 ዓ/ም ከቻርተሩ የመነጩ ህግ የማውጣትና አስፈፃሚ አካላትን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን ይዞ ከሶስቱ የመንግስት አካላት አንዱ ህግ አወጭ አካል ሆኖ ተመስርቷል፡፡ ይህ ምክር ቤት እንደተመሰረተ ባለፉት ሁለት የምርጫ ወቅቶች የገጠሙትን ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች አልፎ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዓመት ዓመት ራሱን በአሰራር፣በአደረጃጀትና በግብዓት እያደራጀ እና እያሻሻለ በመምጣቱ አሁን ላይ ውጤታማ ስራ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡
አሁን 3ኛ ዙሩን የያዘው ም/ቤታችን 138 አባላትን ያሉት ሲሆን በሁለቱ ዙር ከነበሩ የም/ቤት አባላት የተሻለ አቅም እና ብቃት ያላቸው የከተማውን ነዋሪ በሚመጥኑ አካላት ተደራጅቷል፡፡ የሴቶች ተዋፅኦ 50% ለማድረስም የተሞከረበት ሲሆን የአባለቱን የሙያ ስብጥር ታሳቢ ያደረገም አደረጃጀት ለመፍጠርም የቻለ ነው፡፡ በመሆኑም በዘንድሮው አመት ምስረታ ያገኘው የአዲስ ምዕራፍ ም/ቤት ተልዕኮውን ለማሳካት ያለው ተነሳሽነት እና ብቃት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

በመሆኑም ሁለቱን የም/ቤት ተልዕኮዎች ማለትም ህግ የማውጣትና አስፈፃሚ አካላትን የመከታተል የመቆጣጠርና የመደገፍ ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ይህንንም በተጨባጭ ለማሳካት ይችል ዘንድ ባለፉት ወራት በሂደቱ ማነቆ የሆኑ ደንቦችና መመሪያዎችን የማሻሻል፤ አደረጃጀቶች የመፈተሽና የማስተካከል፣ግልጽና ሊያሰራ የሚችል ዕቅድ በማዘጋጀት ተልኮውን በአቅም መፈጸም እንዲችል ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ይህ አሰራርም እስከ ታችኛው መዋቅር እንዲወርድና ሁሉም የም/ቤቱ መዋቅሮች ተመሳሳይ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡
በአብዛኛው የከተማችን ነዋሪ እንደሚታወቀው ም/ቤቶች የህዝብ ጥያቄዎች የሚስተጋባባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ይህን ተግባር በሚፈልገው ደረጃ ለመወጣት ደግሞ ም/ቤቱና ህዝቡ ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም በከተማዋ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ሂደት በጋራ እንድንሰራ ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
በመጨረሻም በም/ቤቱ ያሉ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን በዚህ ድረ-ገጽ ላይ እና በተለያዩ መንገድ ተደራሽ የምናደረግ መሆኑን እየገለጽኩ የመረጃ ልውውጥ ሂደቱ ውጤታማ ይሆን ዘንድ አስተያየት እና ጥቆማዎችን የምታደርሱበትን አማራጮች በመዘርጋት ለጋራ ለውጥ በጋራ የምንሰራ መሆናችንን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!!